መልአከ ገነት ቆሞስ አባ አብርሃም ገ/ሚካኤል
የደብሩ አስተዳዳሪ
“ምሕረኒ እግዚኦ ፍኖተ ጽድቅከ፣ወእኅሥሣ በኩሉ ጊዜ”
“አቤቱ የእውነትህን መንገድ አስተምረኝ፣ ሁልጊዜም እፈልጋታለሁ።” መዝ 118-30
ይኽንን በይነ መረብ ለምታዩልን አባቶቻችንና ምዕመናን ወምዕመናት ሁሉ እንኳን ወደ እኛ ዝግጅት መጣችሁልን በሚል ልጀምረውና መቼም እንደምታውቁት በዛሬ ጊዜ ልማር ላለና በአንሰሃስሆ መንፈስ ቅዱስ ለተነቃቃ ሁሉ መምህራኑ ወደ ነበሩበት የርቀት ዘመንና ቦታ መሄድ ሳያስፈልገው እነርሱ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ በሰጠው ጥበብ/Technology/አማካኝነት በድምጽና በጽሁፋቸው እኛ ወዳለንበት ጊዜና ቦታ እየመጡ ስለሆነ ከስንፍና እና ከድካም በቀር የመምሕራንና የትምህርት ችግር በተለይም እንደልብ የቴክኖሎጂው ፍሰት ባለባቸው አህጉራት ለምንኖረው ምክንያት አይሆነንም!!
በመጽሐፈ ፊልክስስዮስ ላይ ከተፃፈው የአበው ታሪክ ውስጥ አባታችን ታላቁ መቃርስ በአንድ ወቅት አንድ ሴት ወደ እርሱ ዘንድ ለቡራኬ መጥታ በጥልቀት ወደ እርሱ ስትመለከት አፍሮ አንገቱን ሰበር አድርጎ መሬት መሬት ማየት ጀመረ ይለናል። ሴትዮይቱ አባታችን ስለምን ምክንያት ወደ መሬት ታያለህ?ብትለው እርሱም መልሶ አንቺስ ስለምን እንዲህ አድርገሽ ወደ እኔ ትመለከቻለሽ? በማለት እንዳጎነበሰ ጥያቄዋን በጥያቄ መለሰላት። እርሷም እንዲህ አለችው ፟ሴት ከወንድ ተፈጥራለችና እኔ ወደ አንተ አየሁ!አንተ ከአፈር ተፈጥረሃልና መሬት መሬት አየህ! ፟ አለችው ይኽም አባት ከዚህች ተራ ምዕመን ያገኘውን ትምህርት በዘመኑ ከሚያውቃቸው መምሕራን ይልቅ ቁም ነገሩን ልቆ ስላገኘው በኖረበት ዘመን ሁሉ መሬት መሬት እያየ መሄድን *አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ* ከሚለው ለአባታችን አዳም ከተነገረው ጥቅስ ጋር አመሳስሎ ለትህትናና ለእዝናት የሕይወቱ መመሪያ አድርጎት ኖሯል ይለናል።
መቼም ካስተዋልንና ካልናቅን ብዙ ነገር ባነበብንና ባወቅን ቁጥር ለራሳችን ረብ የሚሆን ጥሩ ነገሮችን እናከማቻለን። ጽሁፎች ታላላቅ መመህራን ያስተማሩባቸው የማይታጠፉ ጉባኤያት ናቸው። ካነበብን እንማራለን ለንስሃም እንነሳሳለን።በአብዛኛው ማየት ላይ የተመረኮዙ ልምዶቻችንን ወደ ንባብ ፋታ ውስጥ ብናስገባቸው በሌላ እይታ ውስጥ ያሉትን ቁልፍ ምስጢሮች ለአእምሮአችን መመገብ እንችላለን።
የኛ ዝግጅት በደብራችን ዙሪያ ላሉ ምዕመናን ያሉንን ለማካፈል የጀመርናት እንደመሆኗ በታላላቅ ልሙዳን ከሚመሩት ጋር አትወዳደርም ነገር ግን ያለ ውልደት ልደት ያለ ልደትም ዕድገት የለም እና በውስጡ ለተሳታፊዎች በሚኖረው መድረክ ለአዘጋጆቹ የምታበረክቱት ካላችሁ ቤታችሁ ነው እነሆ *ዚአየ ለዚአከ ዚአከ ለዚአየ* እያልን የእግዚአብሔርን ቃል እንማማር እላለሁ።